ፈውስ ትኩረት ለተነፈጉ በሽታዎች ኢኒሺዬቲቭ (DNDi) እና አጋሮቹ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ፣ አስተማማኝ፣ ለአጠቃቀም ቀላል እና ለህሙማን ምቹ የሆነ በአፍ የሚወሰድ የካላዛር መድሃኒት ለማስገኘት የሚያካሂዱት ምርምር ወደ ምእራፍ ሁለት የክሊኒካል ሙከራ መሸጋገሩ ተገለጸ፡፡
አዲሱ የካላዛር ህክምና የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በሽታውን ለማጥፋት ካስቀመጠው አቅጣጫ ጋር የተጣጣመ እንዲሁም በእጅጉ ትኩረት የተነፈገውንና ለማከምም አስቸጋሪ የሆነውን የካላዛር በሽታ ለማዳን በሚደረገው ርብርብ ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት ያግዛል ተብሏል፡፡
ካላዛር ወይም በሳይንሳዊ ስሙ ቪሴራል ሌሽመናይስስ ከወባ ቀጥሎ በዓለም ላይ በጥገኛ ተህዋሲያን የሚተላለፍ ገዳዩ በሽታ ነው፡፡
በአፍሪካ አሁን እየተሰጠ የሚገኘው የካላዛር ህክምና በሆስፒታል ውስጥ በየቀኑ ለ17 ቀናት የሚወሰድ ከፍተኛ ህመም የሚፈጥር ክትባት ሲሆን ልብን፣ ጉበትን እና ቆሽትን በመጉዳት ለህይወት አስጊ የሆኑ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ሊያስከትል ይችላል። በአንፃሩ በኢትዮጵያ በምርምር ላይ የሚገኘው አዲሱ የ“LXE408” በአፍ የሚወሰድ መድሀኒት አሁን ከሚሰጠው ህክምና የበለጠ ፈዋሽና አስተማማኝ እንደሚሆን ይጠበቃል።
“ኢትዮጵያ እንደ አንድ ካላዛር የተንሰራፋበት አገር፣ አዳዲሶቹ ኬሚካላዊ ምርምሮች ወደሚካዱበት ምእራፍ ሁለት ክሊኒካዊ ሙከራ መግባቷ ትልቅ እምርታ ነው፡፡ ይህ ምርምር ውጤታማና ደህንነቱ የተጠበቀ ህክምና የማስገኘት እድሉ ሰፊ ነው፡፡” ይላሉ ዶ/ር እሌኒ አየለ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የካላዛር በሽታ ጥናትና ህክምና ማዕከል ውስጥ በሚካሄደው በዚህ ክሊኒካል ሙከራ ተባባሪ ተመራማሪ።
“አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያሉት የካላዛር ህክምና አማራጮች ከፍተኛ የሆነ ውስንነት ያለባቸው፣ ጎጂ ክትባትን ግዴታ የሚያደርጉ፣ እጅግ ቀዝቃዛ የህክምና ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ የሚውሉባቸው እንዲሁም ህሙማን አገልግሎቶቹን ፍለጋ የረጅም ርቀት ጉዞ የሚጠይቁ እና ለረጅም ጊዜም ሆስፒታል ውስጥ ተኝተው የሚታከሙባቸው ናቸው፡፡” ይላሉ ተመራማሪዋ፡፡
“እቅዳችን ከሰመረልን በምርምር ላይ የሚገኘው ህክምና ፈዋሽ፣ የጎንዮሽ ጉዳቱ አነስተኛ የሆነና ህሙማን በመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ በሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማት ተደራሽ ይሆናል፡፡ ይህም ህክምናው ባስፈለገበት ጊዜ ሁሉ ታካሚዎች በቀላሉ እንዲያገኙትና የበሽታውን ተስፋፊነትና ጉዳት ይቀንሳል። ከምንም በላይ በሽታውን እስከወዲያኛው ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል፡፡” ብለውዋል፡፡
አዲሱ ህክምና በኢትዮጵያ የመድሃኒት ሙከራ መስፈርት መሰረት የሚካሄድ ሲሆን በየቀኑ የሶዲየም ስቲቦግሉኮኔት እና ፓሮሞማይሲን ድብልቅ መርፌዎች ለ17 ቀናት ይሰጣል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከ18 እስከ 44 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 52 ፈቃደኛ ጎልማሶች በጥናቱ ይሳተፋሉ ተብሏል።
ተመሳሳይ የሁለተኛው ምእራፍ የ”LXE408” ክሊኒካዊ ሙከራ በህንድ አገር እየተከናወነ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካና ደቡብ እስያ የሚገኙ ህሙማን ለዚህ ምርምር የተለያየ ምላሽ እነደሚያሳዩ ይጠበቃል፡፡ ይህ የተለያየ ምላሽም ነው ተገቢው ህክምና እንዲገኝ ምርምር ማካሄዱን የግድ ያደረገው፡፡
“በካላዛር ሕክምናዎች ወደ አዲሱ ትውልድ የህክምና አሰጣጥ እየተሻገርን እንገኛለን። በሽታውን በዘላቂነት ከመላው አለም በተለይም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ከሆኑት የአፍሪካ አገራት ለማስወገድ አዳዲስ ሕክምናዎችን ማግኘት መሰረታዊ ነገር ነው። ይህ አዲስ ክሊኒካዊ ሙከራም የተሻለ፣ ለታካሚ ተስማሚ፣ ለሁሉም ሰው ተደራሽ የሆኑ ውጤታማ መድሃኒቶችን ለማስገኘት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተስፋ እናደርጋለን።” ብለዋል ዶ/ር ፋቢያና አልቬዝ በዲኤንዲ የካላዛር ፕሮግራም ዳይሬክተር፡፡
ይህ በአፍ የሚወሰድ “LXE408” የተሰኘ ህክምና ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በአለም አቀፉ መድሃኒት አምራች ኩባንያ በኖቫርቲስ (Novartis) ነው። ከዚያም እ.አ.አ በ2020 መጀመሪያ ላይ ዲኤንዲ እና ኖቫርቲስ እንክብሉን በጋራ ለማበልጸግ የትብብር ስምምነት ፈጽመው በአንድ ማእቀፍ መስራት ጀመሩ። የቅድመ ክሊኒካዊ ምርምርን እና የመጀመሪያ ደረጃ ጥናትን የማጠናቀቅ ብሎም የኬሚካል ምርትና ቁጥጥር ስራውን ሃላፊነት ወስዶ እየሰራ የሚገኘው ኖቫርቲስ ሲሆን ምርመሩ ውጤታማ ሆኖ መድሀኒቱ የገበያ ፍቃድ ካገኘም የተጠቃሚውን አቅም ባገናዘበ ዋጋ በአለም አቀፍ ደረጃ ለገበያ ያቀርባል፡፡ በመሆኑም በዋናነት በሽታው በእጅጉ የተንሰራፋባቸው አገራት ተደራሽ ይሆናሉ።
የ“LXE408” ህክምና ግኝት እና ህክምናውን በክሊኒካዊ ምርምር በማዘመን የካላዛር ህሙማንን ለመርዳት የሚደረገው ጥናት በብሪታንያው ግብረሰናይ ድርጅት ዌልካም የገንዘብ ድጋፍ የተካሄደ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተካሄደው ክሊኒካዊ ሙከራ ደግሞ የገንዘብ ድጋፉን ያገኘው ከአውሮፓና በማደግ ላይ ያሉ አገራት ክሊኒካዊ ሙከራዎች ጥምረት (EDCPT) ነው።
በአሁኑ ጊዜ፣ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ወቅት እየጠበቀ እንዳዲስ የሚቀሰቀሰውን የካላዛር በሽታ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ እቅድ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ይህን እቅድ ለማሳካትና በሽታው ዳግም እንዳይመለስ የሚደረገው ጥረትም የተሻሻሉ ህክምናዎችን በመተግበር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ውጤቱ ያማረ ከሆነ፣ አዲሱ በአፍ የሚወሰድ ህክምና “LXE408” ይህን በሽታውን የማስወገድ ጥረት በእጅጉ ያግዛል፡፡
“ካላዛር ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን በዋናነትም ህጻናትን የሚያጠቃ ለህይወት አስጊ የሆነ በሽታ ነው፡፡ ይህን በሽታ ባስቸኳይ ልናስወግደው ይገባል፡፡ ይህን ማሳካት የበሽታው ተጠቂ የሆኑትን ማህበረሰቦች ከድህነት ልማውጣትም ሁነኛ መንገድ ነው፡፡” ብለዋል በተ/መ/ድ የጤና ድርጅት ሳይንቲስትና የካላዛር በሽታ መከላከል ተጠሪ ዶ/ር ሳዉራብ ጃይን።
“በ2030 አንዱ አላማችን ለህብረተሰብ ጤና ጠንቅ የሆኑትን ትኩረት የተነፈጉ የትሮፒካል በሽታዎች በዋናነትም ካላዛርን ማስወገድ ነው፡፡ በዚህ መሰረት የተሻሻሉ ምርመራዎችንና ህክምናዎችን ማካሄድ ከዋናዋናዎቹ ተግባራት አንዱ ነው።” ብለዋል።
ለዚህ ጥናት የገንዘብና ተክኒካዊ ድጋፍ የተገኘው ከአውሮፓና በማደግ ላይ ያሉ አገራት ክሊኒካዊ ሙከራዎች ጥምረት (EDCTP2)፣ ከኖርዌይ የልማት ትብብር ኤጀንሲ፣ የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የጀርመን የትምህርት እና ጥናት ሚኒስቴር፣ ሜዲሲንስ ሳንፍሮንቴርስ ኢንተርናሽናል፣ የስዊዘርላንድ የልማትና ትብብር ኤጀንሲ፣ የብሪታንያ አለም አቀፍ ልማት ድርጅት፣ የተለያዩ የግል ፋውንዴሽኖችና ግለሰቦች ይገኙብታል፡፡
የካላዛር በሽታ ትኩሳት፣ የክብደት መቀነስ፣ ከልክ ያለፈ የጣፊያና የጉበት እድገት ያስከትላል፡፡ በሽታው በጊዜው ካልታከመ ለሞት ሊዳርግም ይችላል፡፡ ካላዛር በአሸዋ ዝንብ ንክሻ የሚተላለፍ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ፣ ደቡብ እስያ እና ደቡብ አሜሪካ በሚገኙ 80 አገራት ውስጥ ተንሰራፍቷል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ለዚህ በሽታ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር አንድ ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን አብዛኞቹ ህሙማንም በምስራቅ አፍሪካ ይገኛሉ።
የአየር ንብረት ለውጥ የካላዛር በሽታን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በማወክ በሽታው እስካሁን ወዳልተዳረሰባቸው ቦታዎች እንዲስፋፋ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በአለም ላይ በየአመቱ ከ50,000 እስከ 90,000 የሚደርሱ ሰዎች በካላዛር የሚያዙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ገሚሱ እድሜያቸው ከ15 አመት በታች የሆኑ ህጻናት ናቸው፡፡
ስለ ዲኤንዲ
ዲኤንዲ ለትርፍ ያልተቋቋመ የጤና ምርምር ድርጅት ሲሆን ትኩረት ለተነፈጉ ታካሚዎች፣ ቻጋስ በሽታ ላለባቸው፣ እንቅልፍ ሕመም (አፍሪካዊ ትራይፓኖሶሚስ)፣ በካላዛር፣ በፋይላር ኢንፌክሽን፣ ማይሴቶማና ሄፓታይተስ ሲ ለሚሰቃዩ እንዲሁም በኤችአይቪ ለተጠቁ ሕፃናት የተሻሻሉ ህክምናዎችን ለማቅረብ ይሰራል። በአፍሪካ ከቀላል እስከ መካከለኛ ለሆኑ የኮቪድ-19 ጉዳዮች ሕክምና ለማግኘት የጸረ-ኮቪድ ክሊኒካዊ ሙከራን በማስተባበር ላይም ነው። ዲኤንዲ ከተቋቋመበት እኤአ 2003 ዓ/ም ጀምሮ ዲኤንዲ በአለም ዙሪያ ካሉ የህዝብ እና የግል አጋሮች ጋር በመሆን አስራ ሶስት አዳዲስ ህክምናዎችን በማቅረብ የሚሊዮኖችን ህይወት ታድጓል።
ለተጨማሪ መረጃ፦
የምስራቅ አፍሪካ ዲኤንዲ (DNDi) ጽ/ቤት – ናይሮቢ
Linet Otieno
+254 733 624 206
latieno@dndi.org
ጄኔቭ
Frédéric Ojardias
+41 79 431 62 16
fojardias@dndi.org
Photo credit: Sydelle Willow Smith-EDCTP